“በክልሉ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሥራዎችን በመደገፍ የልማት ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ ነው” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)።
ደሴ:ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ እና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ የሠራቸውን ልዩ ልዩ ማሽኖች ለክልሉ ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ የማስረከብ ሥነ ሥርዓት በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል።
የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ እና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዘላለም በላይ ኢንተርፕራይዙ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ማሽኖችን በማምረት ለተጠቃሚዎች በማቅረብ የኅብረተሰቡን ሥራ እያቃለለ ይገኛል ብለዋል።
በተለይ በቴክኖሎጂ የታገዙ ማሽኖችን በመሥራት፣ በማላመድ እና በማስፋት የእርሻ ትራክተሮችን ጭምር በመገጣጠም የግብርና ዘርፉንም ለማዘመን እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በኢንተርፕራይዙ የተሠሩ 117 የእንጨት መሰንጠቂያ፣ የበቆሎ መፈልፈያ፣ የሞተር ማሽን እና ቱል ግራይንደር ማሽኖችን ዛሬ ለክልሉ ሥራና ሥልጠና ቢሮ ማስረከባቸውን ተናግረዋል።
ማሽኖቹ የተግባር ተኮር ሥልጠናዎችን የሚያጠናክሩ፣ የኢንዱስሪ እና የግብርና ሥራዎችን የሚያዘምኑ ብሎም ፈጣን መኾናቸውን የተናገሩት የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያ (ዶ.ር) ናቸው።
ኀላፊው የተረከቧቸውን ማሽኖች ለተደለደለላቸው የቴክኒከ እና ሙያ ኮሌጆች በማስረከብ የንድፈ ሃሳብ ሥልጠናን በተግባር ለማስደገፍ የላቀ ሚና እንደሚኖራቸው ነው ያረጋገጡት።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ እና የኢንተርፕራይዙ የቦርድ ሠብሣቢ ጥላሁን መሐሪ (ዶ.ር) በበኩላቸው ኢንተርፕራይዙ ዘመኑን የዋጀ የተሻለ አሠራር እንዲኖረው ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ተቋሙ የተቋቋመበትን ዓላማ እንዲያሳካ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡
በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በክልሉ የብልጽግና የልማት ጉዞን ለማሳካት የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ማሽን ቴክኖሎጅ የላቀ ሚና እንዲወጣ የነበሩበትን ችግሮች በመፍታት እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
በክልሉ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሥራዎችን በመደገፍ እና በማበረታታት የብልጽግና ልማት ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡
በተለይ የተለያዩ ተቋማትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ኅብረተሰቡን በተሻለ ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችሉ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል።
ለፈጠራ እና ለቴክኖሎጂ ሥራዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ በመደገፍ እና በማሳደግ ውጤታማ እንዲኾኑ የክልሉ መንግሥት ጥረት ያደረጋል ብለዋል፡፡
የክልሉ የልማት ድረጅት የኾነውን ኢንተርፕራይዝም በመደገፍ እና የገበያ ትስስር በመፍጠር የኅብረተሰቡን ሥራ እንዲያዘምን ብሎም የመጭውን የሀገሪቱን የቴክኖሎጀ ሽግግር እንዲያሳልጥ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል፡፡
በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ የክልል፣ የዞን፣ የከተማ መሪዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የአሚኮ እንደዘገበው





All reactions:
2929
Views: 2
